Рет қаралды 17,174
የባቄላ ቅርፅ ያላቸው ሁለቱ ኩላሊቶቻችን እያንዳንዳቸው የእጃችንን መዳፍ ያህል ያክላሉ፡፡ ኩላሊቶቻችን በሰውነታችን ውስጥ ብዙ ስራ ይሰራሉ፡፡ ከነዚህ መካከል
በሰውነታችን ውስጥ ያለ ቆሻሻ እና ትርፍ ፈሳሽ በሽንት መልክ ያስወግዳል
የሰውነታችንን የደም ግፊት መጠን ይቆጣጠራል
ጤነኛ አጥንት እንዲኖረን ቫይታሚን ዲ ያመርታል
የቀይ የደም ሤል ምርትን ይቆጣጠራል
የኩላሊት ችግር ወይም ህመም ምልክቶች ምን ምን ናቸው?
የኩላሊት ህመም የተለያዩ የህመም ምልክቶች ይኖሩታል፡፡ ምልክቶቹ ከሰው ሰው ቢለያዩም ባብዛኛው ግን
የሽንት መብዛት ወይም ማነስ
አረፋማ ሽንት ወይም ደም ያለበት ሽንት
ቶሎ ቶሎ ሽንት መምጣት
ሽንታችን ቀይ ወይም ቡናማ ከሆነ
ድካም እና ትኩረት ማጣት
የቆዳ መድረቅ እና ማሳከክ
የእግር እና የቁርጭምጭሚት ማበጥ
ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ
የምግብ ፍላጎት ማጣት
ለኩላሊታችን ጤና
1. የሰውነታችንን የስኳር መጠን መቆጣጠር፡- ግማሽ ያህል የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች የኩላሊት ህመም ይደርስባቸዋል፡፡ ስለዚህ በተቻለ አቅም የስኳር ህመም እንዳይዘን መጠንቀቅ አለብን፡፡ የስኳር ህመም ካለብን ደግሞ ቶሎ ቶሎ የኩላሊታችንን ጤንነት መመርመር አለብን፡፡ ምክንያቱም በስኳር ህመም ምክንያት የሚመጣ የኩላሊት ችግር በጊዜ ከተደረሰበት መዳን ይችላል፡፡
2. መድሃኒቶችን በጥንቃቄ መወሰድ፡- ለህመም ማስታገሻ የሚውሉ መድሃኒቶችን ለረጅም ጊዜ በብዛት መውሰድ ኩላሊታችን ላይ ችግር ያስከትላል፡፡ ስለዚህ በብዛት መውሰድ የለብንም፡፡ ካለብን የጤና እክል አንፃር እንደዚህ አይነት መድሃኒቶችን በተደጋጋሚ መውሰድ ካለብን ከሃኪማችን ጋር በመነጋገር ቶሎ ቶሎ የኩላሊታችንን ጤንነት መመርመር አለብን፡፡ በተጨማሪም ለህመሞች የሚታዘዙልንን መድሃኒቶች በሃኪም ትእዛዝ እና በስነሰርአት መውሰድ አለብን፡፡
3. የደም ግፊታችንን መቆጣጠር፡- የደም ግፊት በሽታ ለስትሮክ ወይም ለልብ ድካም ችግሮች ያጋልጣል፡፡ በተጨማሪም ኩላሊታችንን በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳል፡፡ጤነኛ ሰው የደም ግፊቱ 120/80 ነው መሆን ያለበት፡፡ የደም ግፊታችን ከዚህ ከተለየ ግን ሃኪም ማማከር እና የሚሰጠንን ህክምና እና ምክር በደንብ መከታተል አለብን፡፡ የደም ግፊት ችግር በተለይ ከኮሌስትሮል ወይም የልብ ህመም ወይም የስኳር ህመም ጋር ከተዳበለ ኩላሊታችንን ሊያበላሸው ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፡፡
4. ጤናማ መሆን፡- ብዙ ጊዜ ኩላሊታችን በሌላ ህመም ወይም ለሌላ ህመም በሚሰጥ ህክምና ምክንያት ይጎዳል ወይም ይታመማል፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ጤናችንን ለመጠበቅ መጣር አለብን፡፡ በተቻለ አቅም አትክልት፤ ፍራፍሬ እና ጥራጥሬዎችን መመገብ፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እና ጨው አለማብዛት/መቀነስ ይመከራል፡፡
5. ውሃ መጠጣት፡- ውሃ መጠጣት ከኩላሊታችን ውስጥ ሶዲየም፤ ዩሪያ እና ቆሻሻ ያስወግዳል፡፡ለዚህ ነው የኩላሊት ጠጠር የተገኘባቸው ሰዎች ብዙ ውሃ እንዲጠጡ የሚመከሩት፡፡ በቀን ውስጥ አንድ ሰው መጠጣት ያለበት የውሃ መጠን የሚወሰነው በፆታው፤ በአየሩ ሁኔታ፤ እርግዝና ወይም ጡት ማጥባት ካለ፤ የጤናው ሁኔታ እና በሚያደርጋቸው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ነገር ግን በቀን ከ 1.5 ሊትር እስከ 2 ሊትር ውሃ መጠጣት ጥሩ ነው ተብሎ ይመከራል፡፡
6. ከታሸጉ መጠጦች እና ምግቦች መራቅ፤- የታሸጉ ምግቦች ማለትም የድንች ጥብስ፤ ለስላሳ፤ ብስኩት እና የመሳሰሉት ብዙ ስኳር ወይም ብዙ ጨው ይኖርባቸዋል፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን እነሱን አለመመገብ፡፡
7. የአልኮል መጠጥ እና ሲጋራ መቀነስ/ማቆም፡- አልኮል እና ሲጋራ ብዙ ጉዳት በጤናችን ላይ ያደርሳሉ፡፡ ለምሳሌ ሲጋራ የደም ስሮቻችን እንዲጠቡ በማድረግ ወደ ኩላሊታችን የሚገባውን የደም መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ሲጋራ እና አልኮል ብንቀንስ ወይም ብናቆም ለኩላሊታችን ጠቃሚ ይሆናል፡፡
የኩላሊት ችግር በጊዜው ከተደረሰበት የመዳን እድሉ ከፍ ያለ ነው፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን አመታዊ የጤና ምርመራ ስናደርግ ኩላሊታችን ጤነኛ መሆኑን ብንመረመር ጥሩ ይሆናል ነገር ግን
የስኳር ህመም ካለብን
የደም ግፊት ህመም ካለብን
ውፍረት ካለ
በቤተሰባችን ውስጥ የኩላሊት ችግር ካለ ከሃኪማችን ጋር በመማከር ቶሎ ቶሎ ኩላሊታችን ጤነኛ መሆኑን መመርመር ይኖርብናል፡፡
ለጤናዎ የሚጠቅሙ ፅሁፎችን ለማንበብ ገፃችንን ላይክ ያድርጉ
#Ethiopia #Health #Kidney