Рет қаралды 45,914
ኪዳነምህረት መዝሙር | KIDANE MIHRET MEZMUR 31 OCT 24
ኪዳነ ምህረት: የድኅነት ምክንያት ቃል ኪዳንሽ ባይኖር ኖሮ የጥፋት እሳት ባጠፋን ነበር!
Posted on February 20, 2019 by ዲን ዶር ብሩክ ደሳለኝ
ኪዳን ምንድን ነው?
እግዚአብሔር አምላክ ዓለሙን ከፈጠረ ጀምሮ ፍጥረታቱን ሁሉ በቸርነቱ በርኅራሄው ይጠብቃል፤ ይመግባል፡፡ የሰው ልጆች ህግን በመተላለፍ፣ ኃጢአትን ሰርተው እግዚአብሔርን ባሳዘኑ ጊዜ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ዝለው ከእርሱ ከልዑል እግዚአብሔር በረከት ጥበቃ እንዳይርቁ ስለባለሟሎቹ ቅዱሳኑ ብሎ በቃል ኪዳኑ ይጠብቃል:: እግዚአብሔር ከከባለሟሎቹ ጋር የሚያደርገው ቃል ኪዳን የቸርነቱን ብዛት ከሚገልጥባቸው መንገዶች አንዱ የሆነ ፍኖተ እግዚአብሔር ነው:: ‘ኪዳን’ በግእዙ ‘ተካየደ’ ትርጉሙም ተማማለ፣ ቃል ኪዳን ተጋባ ማለት ሲሆን እግዚአብሔር አምላክም ከመረጣቸው ቅዱሳኑ ጋር የገባው ውል ‘ቃል ኪዳን’ ይባላል:: ቃል ኪዳን ማለትም ‘ውል፣ ስምምነት’ ማለት ነው። በዚህች የአስተምህሮ ጦማር እግዚአብሔር አምላክ ፍጥረቱን በምህረቱ የሚጠብቅበትን ‘ቃል ኪዳን’ ከቅዱሳት መጻሕፍት አንጻር እንማራለን:: በተለይም ከቃል ኪዳን ሁሉ የከበረች ስለሆነች በየዓመቱ በየካቲት ፲፮ ስለምናስባት ከ፴፫ቱ የእመቤታችን በዓላት ከሆኑት አንዷ ስለሆነች የእመቤታችን የቃል ኪዳን ዕለትን በተመለከተ እንዳስሳለን::
ቅዱሳት መጻሕፍት እግዚአብሔር አምላክ ከመረጣቸው ከወዳጆቹና ከባለሟሎቹ ከቅዱሳኑ ጋር በየዘመናቱ የፈጸማቸው ኪዳናት እንደነበሩ ያስተምሩናል:: በነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት መዝሙር “ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ:- ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ” (መዝ.፹፱፡፫) ተብሎ እንደተጻፈ እግዚአብሔር አምላክ በበደላችን ምክንያት እንዳንጠፋ የሚጠብቀን በዚሁ ቃል ኪዳን አማካኝነት ነው። ለምሳሌ ምድርንና ሥጋ ለባሹን በንፍር ውኃ ዳግመኛ ላያጠፋ ለአባታችን ለኖኅ ቃል ኪዳን ገብቶለታል (ዘፍ.፱፡፩-፲):: ለቀደሙት አባቶችም ለእነ አብርሃም ለቅዱስ ዳዊት ቃል ኪዳን ገብቷል፤ መሃላንም አድርጓል: (ዘፍ.፳፪፡፲፰ ዘፍ.፳፮፡፬ መዝ.፹፱፡፫):: ይህም ቃል ኪዳን እንደ ተርታ ውል ያለ ሳይሆን የፀና የምህረት ቃል ኪዳን ነው:: በብሉይ ኪዳን የተፈጸሙት ኪዳናት በዓመተ ፍዳ የተፈጸሙ ስለሆኑ የመከራውን ጊዜ ያወሳሉ:: በሐዲስ ኪዳን የተፈጸሙት ኪዳናት ደግሞ ዘመነ ምህረትን የሚያውጁና ጸጋቸውም የበዛ አማናዊ ኪዳናት ናቸው። በአንጻሩ ከቅዱሳኑ ጋር ያደረገው ኪዳን በአምላክ ሰው መሆን ፍጻሜን አግኝቷል::
የእግዚአብሔር የምሕረት ቃል ኪዳን ለቅዱሳኑ ከሃይማኖታቸው ጽናት ከፍጹምነታቸውና ከሥራቸው ትሩፋት የተነሳ በቅድስና ክብር አክብሮ ለገድላቸው እንዲሁም በተጋድሎ ላሳለፉበት ቦታ ለረገጡት አፈር ሁሉ በረከታቸው ተርፎ ዛሬ እኛ ምእመናን በየመካናቱ እምነቱን በመተሻሸት በመጠጣት ከቅዱሳኑ በረከት እንሳተፋለንል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ምህረት የባሕርይ ገንዘቡ ነውና ለሚወዱትም ትእዛዙን ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን እንደሚያደርግ በመጽሐፍ እንደተጻፈ ከቅዱሳኑ ጋር ውልን የሚያደርገው እኛን የሰው ልጆችን በቅዱሳኑ በጎ ሥራ ለመጥቀም ፈልጎ ነው (ዘጸ ፳:፪-፮):: “እንዲህም ይሆናል፤ ይህችን ፍርድ ሰምተህ ብትጠብቃት ብታደርጋትም፥ አምላክህ እግዚአብሔር ለአባቶችህ የማለውን ቃል ኪዳንና ምሕረት ለአንተ ይጠብቅልሃል” ዘዳ ፯:፲፪::
ኪዳነ ምህረት
ኪዳነ ምህረት ማለት የምህረት ቃል ኪዳን ማለት ነው፡፡ ይህም ፍጹም ከከበሩ የእመቤታችን በዓላት አንዱ ከልጇ ከወዳጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የማይጠፋ የዘላለም ኪዳን የሰጠበት ዕለት መታሰቢያ ነው፡፡ ታላቁ የነገረ ማርያም መጽሐፍ እንደሚያስረዳን ጌታችን ካረገ በኋላ እመቤታችን ጌታ ወደ ተቀበረበት ጎልጎታ እየሄደች ትጸልይ ነበር:: ከዕለታት ባንዳቸው በየካቲት ፲፮ ዕለት ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ “ልጄ ወዳጄ ሆይ ከሥጋዬ ሥጋ ከነፍሴ ነፍስ ነሥተህ ሰው በመሆንህ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በቻለችህ ማኅፀኔ ከአንተ ጋር ሀገር ለሀገር ስለመሰደዴ መጥተህ ልመናዬን ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ” እያለች ስትጸልይ ጌታችንም ምን እንዲያደርግላት ሲጠይቃት በስሟ ለሚማጸኑ መታሰቢያዋን ለሚያደርጉ ለችግረኛ ለሚራሩ በስሟ ቤተ ክርስቲያን ለሚያንጹ ዕጣን ዘይትና መብአ ለቤተ ክርስቲያን ለሚሰጡ ምሕረትን እንዲያደርግላቸው ጠየቀችው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “መሐልኩ ለኪ በርእስየ ወበአቡየ ወበመንፈስ ቅዱስ ሕያው” ብሎ በየካቲት ፲፮ እለት ቃል ኪዳን ገብቶላታል:: ይህንን ቃል ኪዳን በነሐሴ ፲፮ ቀን ድግሞታል::
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም በየዓመቱ የካቲት ፲፮ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከልጇ ከወዳጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የምህረት ውል ሰምምነት የተቀበለችበት ቀን በታላቅ መንፈሳዊ በረከት ታከብራለች፡፡ ይህ በታላቅ ድምቀት የሚከበረው የኪዳነ ምህረት በዓል ቀድሞ ለነበሩ ኪዳናት ኪዳነ አዳም ኪዳነ ኖህ ኪዳነ አብርሃም ኪዳነ ዳዊት መደምደሚያ ነው፡፡ ለዚህም የማያልፍ የምህረት ቃል ኪዳንን ስለገባላት ኪዳነ ምሕረት የምሕረት የይቅርታ መሐላ ውል ስምምነት እየታሰበ በመዝሙር፣ በማኅሌትና በቅዳሴ ይከበራል፡፡ ምዕመናንም በዚሁ ዕለት በረከትን ከእመቤታችን ከቅደስት ድንግል ማርያም ይቀበላሉ፡፡
ኪዳነ_ምህረት
በየካቲት ፲፮ ዕለት በስንክሳር እንደተጻፈ “መታሰቢያዋን ለሚያደርግ ስሟን ለሚጠራ ለድሆችና ለችግረኞች ቀዝቃዛ ውኃ ለሚሰጥ የክብር ባለቤት ከሆነ ከተወደደ ልጅዋ ከጌታችን ከአምላካችንና ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳንን ተቀብላላች:: በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም የምህረት ቃል ኪዳን ውስጥ “ስምሽን የጠራ” ሲል በጸሎቱ በእርሷ የተደረገለትን የአምላክ ቸርነት እያሰበ ዘወትርና እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ በእምነት ጸንቶ በጎ ምግባርን እየፈጸመ ስሟን የሚጠራ ይድናል ማለቱ ነው፡፡ ቅዱሳን የሰው ልጆችን ልመና እንዲያቀርቡ መላእክቱም የቅዱሳኑን ጸሎት በማዕጠንታቸው እንዲያሳርጉ (ራእ ፰:፫-፬) ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ ነቢዩ ኤልሳዕም የነቢዩ ኤልያስን ስም እየጠራ በመጸለዩ በረከትን አግኝቷል፡፡ የነቢያት ትንቢታቸው፣ የሰማዕታት እናታቸው፣ የመላእክት እህታቸው፣ የሐዋርያት ሞገሳቸው የሆነችው የድንግል ማርያምን ስም አምኖ ለሚጠራት ከዚህ በላይ ድንቅ ያደርጋል፡፡ እርሷ ለዓለማት ፈጣሪ እናቱ ናትና፡፡
“ዝክርሽንም ያዘከረ” ሲል በእርሷ የተደረገለትን ድኅነት እያሰበ፣ በስሟ ለተቸገረ የሚመጸውት የዘላለም ሕይወትን ያገኛል ሲል ነው፡፡ እርሷን እናት ብሎ ያመነና የጠራት ልጅዋንም ወልድ ዋሕድ ብሎ ያምናል ይጠራልና ይህ ቃል ፍጹም እውነት ነው፡፡ “የአምላክ እናት” ብሎ ዝክሯን የሚያዘክር ልጅዋን “አምላክ” ብሎ አምኗልና “ዝክርሽን ያዘከረ ይድናል” የሚለው ቃል ጽኑዕ ነው፡፡ ለቤተክርስቲያን አገልግሎት መባዕን በስሟ የሚሰጡትም እንዲሁ ነው፡፡ ስም መጥራት የማመን የመታመን መገለጫ ነው፡፡ ዝክርን ማዘከርም በእምነት የሚደረግ የትሩፋት ሥራ ነው፡፡ በቅዱሳን ስም የክርስቶስን ቤተክርስቲያን ማሳነጽ ደግሞ ከሁሉ የከበረ የጽድቅ ሥራ ነው፡፡
“በስምሽ ቤተክርስቲያን ያሠራ” የሚለው ሀረግ የምዕመናንን ኅብረት በእምነት ያጸና፣ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የሚፈተትበትን ቤተ እግዚአብሔር ያሳነጸ፣ የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ የሆነውን የሰውን ልጅ የተዋሕዶን ትምህርት አስተምሮ ያሳመነና ያጠመቀ ድኅነትን ያገኛል ማለቱ ሲሆን ይህም በቅዱሳት መጻሕፍት የተቀመጠ እውነተኛው የጽድቅ ሥራን የሚገልጽ ነው፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ምልዕተ ፀጋ ብሎ ያመሰገናት ድንግል የአምላክ እናት እንዲሁም መልዕልተ ፍጡራን በመሆኗ በቅዱሳት መጻሕፍትም ‘ለእስራኤል የማልሁላቸው መሐላ የገባሁላቸው ቃል ኪዳንም ይህቺ ናት" (ኢሳ.፶፱፡፳-፳፩) እንዲሁም በቅዱስ ዳዊት “ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ ስለ አንቺ የተነገረው ነገር ድንቅ ነው”; (መዝ.፹፮:፫) እንዳለ የእመቤታችን ቃል ኪዳን ከሁሉ ኪዳናት ልዩ ነው:: መልዕልተ ፍጡራን የሆነች እመቤታችን ከተመረጡትም ሁሉ በላይ የተመረጠች ናት:: በዚህም ፍጥረታት ሁሉ ተስፋ የሚያደርጓት ምክንያተ ድኅነት አማናዊት የድኅነተ ዓለም ተስፋ ናትና ከሁሉ ኪዳን በተለየ ‘ኪዳነ ምህረት’ ተብላ ትጠራበታለች::