Рет қаралды 16,788
ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች የጻፈው ይህ ደብዳቤ በሁለተኛው የወንጌል ጉዞው ወቅት ነበር፡፡ እንደ 1ኛ ተሰሎንቄ 3፡1-2 አገላለጽ፣ ጳውሎስ በአቴና በነበረበት ወቅት ጢሞቴዎስ ወደ ተሰሎንቄ በመመለስ በዚያ ያሉ አማኞችን እንዲያበረታታ ልኮት ነበር፡፡ ይህም በ49 - 52 ዓ.ም. አካባቢ ማለትም ጳውሎስና ባልደረቦቹ ተሰሎንቄን ለቅቀው ከወጡ በኋላ ነበር፡፡ ምናልባትም በ50 ወይም በ51 ዓ.ም. አካባቢ ጢሞቴዎስ ሲመለስ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ሳይሆን አይቀርም፡፡
በዚያን ጊዜም ጢሞቴዎስ በተሰሎንቄ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተከስተው የነበሩ ብርቱ የግንዛቤ መዛነፎችንና የተፈጠሩ ተግባራዊ ችግሮችን ለጳውሎስ በግልጽ ነገረው፡፡ ጢሞቴዎስም እርሱ ጋ ከደረሰ በኋላ ወዲውኑ ለእነዚህ ጉዳዮች ምላሽ ለመስጠት ሲል ጳውሎስ ከቆሮንቶስ 1ኛ ተሰሎንቄን የጻፈላቸው ይመስላል፡፡ 2ኛ ተሰሎንቄ ግን ከጥቂት ወራት በኋላ፣ ግን ከዚያው ከቆሮንቶስ ተጻፈ፡፡
ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች የጻፋቸው መልእክቶች ከሁለተኛው ሚሲዮናዊ ጉዞው ሰፊ አውድ ጋር እንዴት እንደሚጣጣም ከተመለከትን፣ አሁን ደግሞ በተሰሎንቄ ቤተክርስቲያን የተፈጠሩ ችግሮችን ለየት አድርገን መመልከት ይገባናል፡፡