Рет қаралды 81,206
ቅዱስ ጊዮርጊስ መዝሙር | GIYORGIS MEZMUR
ሊቀ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ማን ነው?
ቅዱስ ጊዮርጊስ የተወለደበት አገር በፍልስጥኤም አውራጃ ውስጥ በምትገኘው ልዳ በተባለች አገር ነው፡፡ ልዳም በሐዋርያት ሥራ እንደተጻፈው ከኢየሩሳሌም ወደ ምዕራብ ከኤማሁስ ቀጥሎ አሥራ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ቅዱስ ጴጥሮስ ቅዱስ ወንጌልን እየዞረ በሚያስተምርበት ዘመን ኤንያ የተባለውን አንካሳ ያዳነባት አገር መሆኑን በሐዋ ሥራ 9፡32 35 ተጽፎ ይገኛል፡፡ ጊዮርጊስ ማለት ኮከብ፣ ብሩህ፣ ሐረገ ወይን፣ ፀሐይ ማለት ነው፡፡ አባቱ በሮም ቋንቋ ዞሮንቶስ በቅብም ቋንቋ አንስጣስዮስ ይባላል፡፡ የእናቱም ስም ቴዎብስታ /አቅሌስያ/ ይባላል፡፡ አባቱ የልዳ መስፍን ነበር፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ በብዙ ባለሟል እንክብካቤ በተድላና በደስታ አድጓል፡፡ ወላጆቹ ፍጹም መንፈሳውያን ስለነበሩ ክርስትናንንም ከሕፃንነቱ ጀምሮ አስተምረውታል፡፡ እድሜው ወደ ሃያዎቹ ሲጠጋ አባቱ በልጅነት ሳለ ስላረፈ የአባቱን ሹመት ለመረከብ ወደ ንጉሡ ዱድያኖስ ዘንደ ሄደ፡፡ ንጉሡ ዱድያኖስ ግን ሰባ ከሚሆኑ ነገሥታት ጋር እየበላና እየጠጣ ይጨፍር ለጣዖትም ይሰግድ ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ንጉሡ ካለበት ሲደርስ ጣዖት አምልኮ ነግሦ ሰው ሁሉ ከእውነተኛይቱ ሃይማኖት ወጥቶ፤ ክርስቲያን ነኝ ማለት ወንጀል እንደሆነ የተነገረውን አዋጅ አይቶና ሰምቶ ተረገመ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ እርሱን ተከትለው የመጡ ባለሟሎችን ካሰናበተ በኋላ የሞቱን መስቀል ተሸክሞ በኋላም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም ነፍሱን ሊያድን የሚወድ የጠፋታል ነፍሱን ስለእኔ የሚያጠፋ ያገኛታል ማቴ 1ዐ፡38 39 በማለት የሕይወት ባለቤት መድኃኔዓለም ክርስቶስ የተናገረውን ቃል መሠረት በማድረግ ኃላፊ ጠፊ የሆነውን ምድራዊ መንግሥት በመተው የማያልፈውን ዘለዓለማዊ ሰማያዊ መንግሥት ተስፋ አድርገው ከጣዖት አምላኪዎች ከአሕዛብ ከመናፍቃን የሚደርሰውን መራራ ሞት ማለትም እሳቱን ስለቱን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ስለ አምላኩ መስክሮ በሰማዕትነት ለማለፍ ወሰነ፡፡ ምድራዊውን ሹመት ተወ፣ ናቀ፡፡ ሰማያዊ ሹመት እንደሚበልጥም አስቦ ሐዋርያዊውአባተ ቅዱስ ፖሊካርፐስ "እኛ የተሻለውን በክፉው አንለውጥም ነገር ግን ክፉውን በመልካሙ እንለውጣለን›› እንዳለ ክፉውን የነዱድያኖስን ኑሮ በመልካሙ ክርስትና ሊለውጥ ተዘጋጀ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለምስክርነተ ቆርጦ መነሳቱን ንጉሡ ሲመለከት አስጠርቶ የሚሰቃይባቸውን መሣሪያዎት አሳየው፡፡ "እነርሱም የብረት አልጋዎች፣ የብረት ምጣዶች፣ መንኩራኩሮች፣ አጥንት ለመስበር የሚችል ከብረት አልጋዎች የእጅ መቁረጫ፣ ምላስ ለመቁረጥ የሚችል ቢለዋ፣ አጥንትን ከጅማት የሚለያይ መውጊያ፣ አእምሮን የሚነሳ ጉጠት፣ አጥንት የሚቀጠቅጡባቸው የተሳሉ መጋዞች፣ አፋቸው እንደ መጋዝ ዋርካ ያለው የብረት ድስት፣ ረዣዥም የብረት በትሮች፣ ጥርስ ያለው የብረት ጐመድ መሣሪያዎች ነበሩ /ገድለ ጊዮርጊስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 8/ ነበሩ፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ይህንን አይቶ አልፈራም፡፡ ለሃይማኖቱ ቀናኢ ነውና ከቤተመንግሥቱ ገብቶ በከሃዲያኑ ሥጋውያን ነገሥታት ፊት ክርስቲያን መሆኑን በመመስከር የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት መሰከረ፡፡ ዱድያኖስም ማንነቱን ከተረዳ በኋላ "አንተማ የኛ ነህ በአሥር አህጉር ላይ እሾምሃለሁ የኔን አማልክተት አጰሎንን አምልክ" አለው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም "ሹመት ሽልማትህ ለአንተ ይሁን እኔ አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስን አልከዳውም" አለው፡፡ ክርስትናውንም በአደባባይ ከመመስከር ወደኋላ አላለም፡፡ ጣዖታት የማይረቡ የማይጠቅሙ የአጋንንት ማደሪያዎች መሆናቸውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከበረ ደሙ ፈሳሽነት መላውን የሰው ዘር ያዳነ እውነተኛ ዘላለማዊ አምላክ መሆኑን አስተማረ፤ ይልቁንም በሚያደርገው አምልኮ ጣዖት ወደ ኩነኔ ወደ ገሃነም እንደሚገባ በግልጽ ነገረው፡፡ ስለዚህ ዱድያኖስ ተቆጥቶ ለሰባት ዓመታታ ለሰሚ የሚደንቅ መከራ አጸናበት ቅዱስ ጊዮርጊስ የደረሰበት እጅግ አሰቃቂ መከራዎች የሰው ኀሊና ሊያስባቸው እንኳን የማይችላቸው ናቸው፡፡ እየፈጩ፣ እየሰነጠቁ፣ በጋለ ብረት እየወጉ አሰቃዩት፡፡ በዚህ ጊዜ ሦስት ጊዜ ሞቶ ተነሳ እግዚአብሔር ጠላቶቹን ድል ሳያደርግ እንዳይሞት ፈቅዶልና ከሞት አስነሳው መከራውን ሁሉ ግን ተቀበለ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እየበረታ የሚያደርሱበትን ስቃይ ደስ እያለው ይጠቀበለው ነበር፡፡ ከፈጣሪው ዋጋ የሚያገኝበት ነውና፡፡ ሉቃስ 6፡22 24
ቅዱስ ጊዮርጊስ ስለ ክርስቶስ ፍቅር ሲል የተቀበለው መከራና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ያደረገው ተአምራት ተጽፎ አያልቅም፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ለማስታወስ ያህል መንገን በተባለው መንኩራኩር ሥጋውን ከአጥንት ጋር ቆራርጦ በሚፈጭ መሣሪያ አስገብተው ሥጋውን ከአጥንቱ ጋር ቆራርጠው አድርቀው ፈጭተው ደብረ ይድራስ በተባለው ተራራ እንደ እህል በነፋስ በትነው ዘርተውታል፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ ከሞት አንስቶ በንጉሡ ፊት እንዲቆም አድርጎታል፡፡ ንጉሡ ዱዲያኖስም ባየው ጊዜ በጣም ደንግጧል አፍሯል፡፡ እንደገና ብረት አንደጫማ አድርገው እንዲራመድ አደረጉት በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ እኮ ከአይሁድ ብዙ ግርፋትና መከራ ተቀብሎ ተሰቅሏል እያለ ይጽናና ነበር፡፡ መላእክትም እየመጡ ያጽናኑት ይረዱት ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአምላኩ በተሰጠው ሥልጣንና ኃይል በንጉሡ ዱድያኖስና በሰብዓ ነገሥታት ፊት በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምኑ ብዙ ምውታን ሴቶችን ወንዶችን ሕፃናትን በአምላኩ ኃይል አስነስቶ አሳይቷቸዋል፡፡ በተለይ በወርሃ ሚያዝያ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ታሪክ የሚናገረው ገድለ ሰማዕት እንደሚያስረዳው ሁለንተና ቅርጹ የብረት ጥርስ ባለው መንኩራኩር ላይ አድርገው ቅዱስ ጊዮርጊስን ስለአገለባበጡት የመንኩራኩሩ ሞተር በዐይኑ በጥርሱ እንዲሁም በመላ የሰውነቱ ክፍል እየገባ ሲገለባበጥ መላው የቅዱስ ጊዮርጊስ አካል እየተበጣጠሰ አለቀ ጊዮርጊስም ሞተ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሞት አስነሳው የቅዱስ ጊዮርጊስ መከራ ሲነሳ ይህን ያህል መወጋቱ፣ መፈጨቱ፣ መዳመጡ፣ መቀጥቀጡ፣ ለምን እንል ይሆናል መቼም ለምስፍና የተጠራ የአንድ አገረ ገዥ ልጅ ለዚያውም ወጣት መከራውን በጸጋ የተቀበለበት ምክንያት ይኖረዋል፡፡ ከእነዚህም የተወሰኑትን ብንመለከት ስለ መንግሥተ ሰማያት ያደረገው መሆኑን እንመለከታለን፡፡ መንግሥተ ሰማያት እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ያዘጋጃት ዘላለማዊ ርስት ናት፤‹‹ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል" ሐዋ ሥራ 14፡22 እንዳለ ስለ ክርስትናቸው በመከራ የተፈተኑ ወደ እርሷ ይገባሉ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጋድሎ የጸናበት አንዱ ምክንያት ይኸው ነው፡፡ እምነቱን በተጋድሎ አጽንቶ ለመንግሥተ ሰማያት ክብር እንዲበቃ ሌላው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያንን ሁሉ መከራ የተቀበለው ሃይማኖቱን ለመመስከር ነው፡፡ ሃይማኖት ማመንንና መታመንን /እምነትንና ተአምኖን/ አጠቃልሎ የያዘ ነው፡፡ ሰው አምኖና ተረድቶ ሲያበቃ ያመነውንና የተረዳውነ በግብር በንግግር መመስከር ግድ ይለዋል፡፡ ጌታችን በሃይማኖት የሚኖሩ በስሙ አምነው የሚጓዙ ክርስቲያኖች ያመኑትን ሊመሰክሩ እንደሚገባቸው ሲያስተምር ከሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ" ብሏል ማቴ 1ዐ፡32 ያመነ እምነቱን ሳያፍር ሳይፈራ ገልጦ እንዲናገር አስተምሯል፡፡ ክርስትና እምነትን መሸሸግ መደበቅ አይደለም የሚያውቁትን መሰወር አይደለም ያመኑትን ላላመኑት ማሳወቅ ነው፡፡ ሃይማኖት ሙሉ የሚሆነው ከምስክርነት ጋር ስለሆነ ክርስቲያን አምኖ መቀመጥ የለበትም ያመነውነ በአደባባይ መመስከር ይገባዋል፡፡ ይህ እውነታ ነው ቅዱስ ጊዮርጊስን በዚያ ዘመን ከሰባው ነገሥታት ጋር ያታገለው ፡፡ በዚህ ዘመን እንኳን ለመመስከር እምነትን በልቡና ሸሽጐ ለመኖር መቻልም ይከብድ ነበር እርሱ ግን ማመን ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ያመኑትን ገልጦ መናገር እንደሚያስፈልግ አውቆ በአደባባይ መሰከረ፡፡ ከዚህ ጽሑፍ የምንማረው ትምህርት ቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣት ሲሆን በዚህ ኃላፊ ዓለም አልተማረክም ሃይማኖቱን ክዶ በዚህ ዓለም ተደስቶ ለመኖር አልፈለገም በሰማያት የሚገኘውን የማያልፈውን ዓለም መረጠ እንጂ፡፡ ስለዚህ በሃይማኖቱ ጸንቶ በአምላኩ ኃይል ብዙ ትአምራት እያደረገ ብዙዎችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምኑና የዘለዓለም ሕይወት እንዲወርሱ አድርጓል፡፡ በመጨረሻም ሰባው ነገሥታት ከድድያኖስ ጋር ሆነው በአምላኮቻችን በጣዕታትና በእኛ ላይ በየጊዜው በኃፍረት ላይ ኃፍረት ጨመረብን ብለው ቅዱስ ጊዮርጊስን አንገቱን በሰይፍ ቆርጠን እንግደለው ብለው ተማከሩ፡፡ ዱድያኖስም ሚያዝያ 23 ቀን አንገቱ በሰይፍ ተቆርጦ እንዲሞት አዘዘ ቅዱስ ጊዮርጊስም በክርስቶስ ስም እንደሚገደል በሰማ ጊዜ በጣም ተደሰተ፡፡